
ኢንተርፕራይዞች ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች በማምረት ተወዳዳሪነታቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ተገለጸ
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተመዘገቡ ምርጥ ተሞክሮዎችን የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው!
EED ሰኔ 15/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን የሚያግዝ የኢንተርፕራይዞች ምርጥ ተሞክሮ ቅመራና ማስፋፋት ስራ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄደ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በመድረኩ እንደገለጹት፤ የአገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች በምርት ሂደታቸው ደረጃውን የጠበቁ አሰራሮችን መከተል እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። ይህም በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው አመላክተዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ቀደም ሲል የአገር ውስጥ ምርቶችን ከተወዳዳሪነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ታሪፎችንና ታክሶችን መጣል እንደ አንድ አማራጭ ይወሰድ እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም አገሪቱ የዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) አባል እየሆነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የፈለጉትን ያህል ታክስ መጣልና ምርቶችን መከልከል የማይቻልበት አሰራር እየመጣ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢንተርፕራይዞች ከወዲሁ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን በመጠቀምና ጥራትን በማስጠበቅ ራሳቸውን ለገበያ ውድድር ማዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አቶ አብዱልፈታ መንግስት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚሰጠውን የብድርና የፋይናንስ ድጋፍ እያሳደገ መሆኑን ገልጸው የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድኑ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚቀርበውን የብድር ድርሻ (ፖርትፎሊዮ) ካለው 12 በመቶ ወደ 20 በመቶ ለማሳደግ ወስኗል።

ይሁን እንጂ ኢንተርፕራይዞች ይህንን የብድር አቅርቦት ለማግኘት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላትና የተሳካ የቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። የልማት መስሪያ ቤቱም ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር የቢዝነስ ፕላንና የባንክ ሰነዶችን በማዘጋጀት ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢንተርፕራይዞች ሌላኛው ትልቅ ማነቆ የግብዓት እጥረት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን ለመቅረፍ ተቋማቱ ከጥሬ ዕቃ አምራቾች ጋር ዘላቂ የሆነ ቀጥታ ትስስር መፍጠር እንዳለባቸው መክረዋል።

በተለይም አብዛኛዎቹ ግብዓቶች ከአግሮ-ፕሮሰሲንግ ጋር የተያያዙና በአገር ውስጥ የሚመረቱ በመሆናቸው፣ ከአገር ውስጥ አምራቾች ጋር የሚደረግ ቀጣይነት ያለው ትስስር ለኢንተርፕራይዞቹ ስኬት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን የቦታ፣ የፋይናንስና የግብዓት ችግሮች ለመፍታት መንግስት የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግና የተሳኩ ተሞክሮዎችን በማስፋፋት የዘርፉን ዕድገት ለማገዝ እንደሚሰራ አቶ አብዱልፈታ በንግግራቸው መደምደሚያ ላይ አስታውቀዋል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት_እኛም_እንሸምት
#ለተጨማሪ_መረጃ_የማህበራዊ_ሚዲያ_ገጾቻችንን ይጎብኙ!
https://linktr.ee/Ethiopianenterprisedevelopment