
ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስትራቴጂ (ረቂቅ) ላይ ውይይት ተካሄደ
EED ግንቦት 02 ቀን 2017 ዓ.ም
ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስትራቴጂ (ረቂቅ) ላይ ውይይት ተካሄደ::
ውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስትራቴጂ ሰነድ በሃገር አቀፍ ደረጃ ወደፊት በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው የልማት መስሪያ ቤቱም ይህንኑ በመገንዘብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የልማት መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር አለባቸው አማካሪ ድርጅቱም በዚያው ልክ ተመልክቶ ሰነዱን ከማዘጋጀት ባሻገር የሚሰጡትን ማስተካከያዎችና ተጨማሪ ሃሳቦች በማካተት የተሟላ ስትራቴጂ ሰነድ ሊያቀርብ ይገባል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ኮንሱል ከተባለው ድርጅት ጋር በጋራ የሚሰራው አይ ከርቭ አማካሪ ድርጅት የአግሮፕሮሰሲንግ ኤክስፐርት ሚስተር ፍሬደሪክ ሄኖ በአማካሪ ድርጅቱ የተዘጋጀውን ረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከተቋቋመውና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ካካተተው ቴክኒክ ኮሚቴ በኩል ደግሞ ማስተካከያዎችና ተጨማሪ ሃሳቦችን በልማት መስሪያ ቤቱ ፔትኮ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አበበ ተካ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል::

በመጨረሻም በጥምረት የማማከር ስራውን እያከናወኑ የሚገኙት ኮንሱል እና አይ ከርቭ በውይይቱ ላይ በተሰጡት ማስተካከያዎች መሰረት አስተካክለው የተሟላ ስትራቴጂ ሰነዱን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያቀርቡ በልማት መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ አቅጣጫ ተሰጥቶ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት_እኛም_እንሸምት