
ልማት መ/ቤቱ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲሆኑ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ
EED መጋቢት 28/2018 ዓ.ም
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከፍተኛ አመራሮች በኦሮሚያ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን ጎብኝተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላትና የልማት መ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተሰማሩና ውጤታማ የሆኑ በተኪ ምርት እና ኤክስፖርት ላይ የተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን ጎብኝተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ተኪ ምርት፣ ስራ እድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግጭት እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ እያደገ መምጣቱን በጉብኝቱ መገንዘባቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲሆኑ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ለኢንተርፕራይዞች ውጤታማነት የሚያስፈልጉ ድጋፎችን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኢንተርፕራይዞች ተወዳዳሪነት ማነቆ የሆኑ የማምረቻ ቦታና የግብዓት አቅርቦት ችግሮች እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅርበት በመስራት ኢንተርፕራይዞችን ማገዝ እንደሚገባ የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ተወዳዳሪና ውጤታማ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች እንዲበራከቱ አስፈላጊው የአሰራር ስርዓት እንዲፈጠርና ተግባራዊ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
በጉብኝት መርሃ ግብሩ በቡና ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማራውና ምርቱን ወደውጭ ገበያ እየላከ የሚገኘው ጭቶ ቡና እና የተለያዩ ማሽኖችን እየመረተ ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ያለው ቴክሶ መካኒካል ኢንጂነሪንግና ሌሎች ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት_እኛም_እንሸምት