ETHIOPIAN ENTERPRISES DEVELOPMENT

Empowering Manufacturing SMEs for National Economic Transformation and Societal Prosperity !

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር፣ ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ

“በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የክትትልና ድጋፍ ስርዓቱ ችግርን የሚፈታና ውጤታማ መሆን አለበት!”

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር፣ ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ

EED ሰኔ 20/2018 ዓ.ም

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚደረገው የክትትልና ድጋፍ ስራ፣ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ የሚያመጣና ዘላቂ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችል ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ አስታወቁ።

ዶ/ር አለባቸው ይህን የገለፁት የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ ዓመት መነሻ ዕቅድ ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው::

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስብስብ የሆኑ ተቋማዊ አሰራሮችን እና ጥምረቶችን የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገው የክትትልና ድጋፍ ስራ ተቋማትን ከመደገፍ ባሻገር ከግንዛቤ መፍጠር ጀምሮ እስከ ማቋቋም እና የመጨረሻውን ምርት ለገበያ ማቅረብ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን መለየት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ተቋማት አቅም ያላቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ፣ አቅም የሌላቸውን ደግሞ ከተለያዩ አካላት ጋር በማስተሳሰር ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግን እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

የዘርፉ ስራ በብቸኝነት ሳይሆን በትብብር የሚከናወን መሆኑን የጠቆሙት  ዶ/ር አለባቸው በተለይም የፋይናንስ አቅርቦት፣ የግብዓት አቅርቦት እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ትክክለኛ የክትትልና ድጋፍ ስራ ለመስራት ዝርዝር እቅድ አስፈላጊ ነው። በተለይም ለእያንዳንዱ የግብዓት ፍላጎት፣ የማምረቻ መሳሪያዎች እና የተቋማት አቅም በተደራጀ መንገድ ማቀድና መተግበር ይገባል።

በአሁኑ ወቅት የክትትልና ድጋፍ ስራው እየተከናወነ ቢሆንም፣ በሪፖርት አቀራረብና በወቅታዊ መረጃ አያያዝ ላይ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ይህንን ለማስተካከል ዲጂታል አሰራርን መጠቀም እና የክትትል ስርዓቱን ዘመናዊ ማድረግ ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

አለም አቀፍ የገበያ ሁኔታዎች እና የሎጂስቲክስ ችግሮች በዘርፉ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አለ። ይህም የዋጋ ንረትን ሊፈጥር ስለሚችል፣ ዘርፉን ከነዚህ ተግዳሮቶች ለመከላከል ስትራቴጂክ ድጋፍ ያስፈልጋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ በቀጣይ የክትትልና ድጋፍ ስራው የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን አቅም በማጎልበት፣ ምርታማነታቸውን ማሳደግ: ግልጽ የሆነ የስራ መመሪያና የክትትል ስርዓት በመፍጠር ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል::

የተቀናጀ አሰራር ለመፍጠር ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ ያለው የዘርፉ አመራር እና ባለሙያዎች ለጋራ ግብ እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባ የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ በማጠቃለያቸው፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ፣ ሁሉም አካላት ለክትትልና ድጋፍ ስራው ትኩረት ሰጥተው በመስራት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

#ለተጨማሪ_መረጃ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻችንን ይጎብኙ!

https://linktr.ee/ethiopianenterprisedevelopment

News