ETHIOPIAN ENTERPRISES DEVELOPMENT

Empowering Manufacturing SMEs for National Economic Transformation and Societal Prosperity !

በስደት ያጠራቀሙትን እውቀትና ገንዘብ ለሀገር ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት፡ አቶ ስምኦን እና የ“ጭቶ ቡና” የስኬት ጉዞ

EED ግንቦት 25/2018 ዓ.ም

ቡና ለኢትዮጵያዊያን መጠጥ ብቻ አይደለም፤ ባህል፣ ታሪክ፣ የማህበራዊ ህይወት መስተጋብርና የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ጭምር ነው። በዚህ ሰፊ የቡና ባህልና ብዝሃ-ህይወት ውስጥ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመናዊ ማኑፋክቸሪንግና እሴት በመጨመር (Value Addition) ረገድ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበና የኢንዱስትሪው አዲስ ተስፋ እየሆነ የመጣ አንድ ስኬታማ የሀገር በቀል ኢንተርፕራይዝ አለ:- ጭቶ ቡና።

ይህ ኢንተርፕራይዝ በልዩ ጣዕሙና በጥራቱ የሚታወቀውን የኢትዮጵያን ቡና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ የሀገራችንን የቡና ገበያ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሊያሸጋግር የሚችል ትልቅ አቅም ይዞ ብቅ ብሏል።

የኢንተርፕራይዙ መስራች አቶ ስምኦን ሰርፁ ይባላሉ። አቶ ስምኦን ለረጅም ዓመታት ኑሯቸውን በውጭ ሀገር አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ የሀገራቸውን ጥሪ ሰምተው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱም ዝም ብለው አልነበረም፤ በማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ በመሰማራት ከፍተኛ ጥራት ያለውና እሴት የተጨመረበትን የኢትዮጵያ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ትልቅ ራዕይ ሰንቀው እንጂ።

አቶ ስምኦንና ጭቶ ቡና ጥሬ ቡናን ዝም ብሎ ከመላክ ይልቅ በዘመናዊ ማሽኖች የተቆላ፣ የተፈጨና የታሸገ ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርት በማዘጋጀት ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ላይ ይገኛሉ። ይህ ጉዟቸው ደግሞ በቅርቡ እጅግ አስደሳች ወደሆነ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፤ ድርጅቱ በቅርብ ጊዜ በትልቁ የዓለም የገበያ መዳረሻ በሆነችው ቻይና ላይ አዲስ ቅርንጫፍ መክፈት ችሏል።

የጭቶ ቡና የዛሬ ስኬት በቀላሉ የተገኘ አይደለም። ጉዞው የጀመረው ከ4 ዓመታት በፊት ነበር። በወቅቱ በነበረው የፍራንኮ ቫሉታ ዕድል በመጠቀም ዘመናዊ የቡና ማቀነባበሪያ ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት፣ ስራቸውን በኪራይ ቤት ውስጥ በጠበበ ቦታ ጀመሩ። ስራ ሲጀምሩም በ5 ሰዎች ብቻ ነበር። ዛሬ ላይ ግን ጭቶ ቡና ያንን የፈተና ጊዜ አልፎ በመስፋፋት ላይ ይገኛል። በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ለገጣፎ የሚገኘውና በጥራትና በዘመናዊ አሰራር ላይ ባደረገው ትኩረት አሁን ላይ ከ40 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የተረጋጋና ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል።

አቶ ስምኦን ስለ ጉዟቸውና ስላጋጠሟቸው እክሎች ሲናገሩ “ችግር የማደግ ምልክት ነው። እኛ ችግሮችን እንደ ፈተና በመውሰድ፣ ፈተናውን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል ብቻ ትኩረት አድርገን እንሰራለን” በማለት የጠንካራ ስራና የዕድገት አስተሳሰብ (Growth Mindset) መርሆቸውን ይገልጻሉ።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የወደፊት ተስፋ
ጭቶ ቡና በአሁኑ ወቅት የቡናውን ተፈጥሯዊ ጣዕምና መዓዛ ሳይለቅ፣ የዓለም አቀፍ ገበያን የጥራት መመዘኛ በሚያሟላ መልኩ እጅግ ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም ምርቱን እያዘጋጀ ይገኛል። ይህ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደግሞ ምርቱ በዓለም መድረክ ተወዳዳሪ እንዲሆን አድርጎታል።

ኢንተርፕራይዙ አሁን ካለበት ተስፋ ሰጪ ደረጃ ተነስቶ ይበልጥ እንዲያድግና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሳድግ ግን የመስሪያ ቦታ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን መስራቹ ሳይጠቅሱ አላለፉም። በቀጣይም የተሻለና ሰፊ የመስሪያ ቦታ ቢመቻችላቸው፣ ይበልጥ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠርና ምርትን በማሳደግ ረገድ ከዚህ የተሻለ የላቀ ውጤት ለማምጣት በትጋት እንደሚሰሩ አቶ ስምኦን ሰርፁ ገልጸዋል።

የጭቶ ቡና ጉዞ ለሌሎች ተመላሽ ዳያስፖራዎችና የሀገር ውስጥ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ትልቅ ማሳያና አምሳያ ነው። በችግሮች ሳይበገሩ፣ ቴክኖሎጂን ከሀገር ምርት ጋር በማቀናጀት የተጀመረው ይህ ጉዞ፣ የኢትዮጵያን ቡና ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርገው ጥርጥር የለውም። ለመሰል ጠንካራ አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚደረግ ማንኛውም ድጋፍ ደግሞ የሀገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የመገንባት ያህል ዋጋ አለው።

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

‎#ለተጨማሪ_መረጃ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻችንን ይጎብኙ!

‎https://linktr.ee/ethiopianenterprisedevelopment

News