
አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በሀገር ዉስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን የምርት ጥራት ደረጃዎች ያሟሉ ምርቶች እንዲያመርቱ በትኩረት እየተሰራ ነው!
EED ሰኔ 11/2018 ዓ.ም
አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች የምርት ጥራት ማረጋገጫ ሰርትፊኬት (Product Certification) እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያግዝ የሰነድ አዘገጃጀት እና አያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠና በተለያዩ ንዑስ ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን ምርታማነትና የጥራት ደረጃ በማሳደግ ኢንተርፕራይዞች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እንዲተኩና ወጪ ምርቶችን እንዲያሳድጉ በማድረግ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ከእነዚህም ስራዎች አንዱ ኢንተርፕራይዞች የምርት ጥራት ደረጃ ሰርትፊኬት እንዲያገኙ በማስቻል በሀገር ዉስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን የምርት ጥራት ደረጃዎች ያሟሉ ምርቶች እንዲመረቱ ማድረግ ነዉ።

በልማት መ/ቤቱ የአግሮ ፕሮሰሲንግ መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ሰለሞን ግዛው እንደተናገሩት ስልጠናው የተዘጋጀው ኢንተርፕራይዞች የምርት ጥራት ማረጋገጫ ሰርትፊኬት እንዲያገኙ ለማስቻል የሚያግዝ በሰነድ አዘገጃጀት እና አያያዝ ላይ ያተኮረ ሥልጠና በመስጠት የኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማጎልበት ነው።
በተመረጡ ኢንተርፕራይዞች አሁን ያለውን የሥራ ሂደት እና የምርት ጥራት አያያዝ ሥርዓትን በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው በዳሰሳ ጥናቱ የመረጃ አያያዝ ላይ ክፍተት በመታየቱ ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
መሪ ስራ አስፈጻሚው አክለውም እያንዳንዱ ተሳታፊ ኢንተርፕራይዝ እንደሚያመርተዉ የምርት አይነት ለራሱ ተስማሚ የሆነ ሰነድ እንዲያዘጋጅና ቀጣይ ሂደቶችን በማሟላት የምርት ሰርትፊኬሽን ማረጋገጫ እስከሚያገኙ ድረስ አስፈላጊውን እገዛም እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

በአመራረትና በመሠረተ ልማት ላይ ያሉ የምርት ጥራት ክፍተቶችን ለይቶ በማወቅ እና አስፈላጊዉን ድጋፍ በመስጠት ኢንተርፕራይዞቹ የምርት ጥራት ማረጋገጫ ሰርትፊኬት እውቅና ካለዉ አካል እንዲያገኙ የማመቻቸት ስራም እንደሚሰራ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አዳራሽ እየተሰጠ በሚገኘው ስልጠና ከአዲስ አበባና ሸገር ከተማ የተውጣጡ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኬሚካልና ቆዳ ዘርፍ የተሰማሩ 24 የሚሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት_እኛም_እንሸምት
ለተጨማሪ መረጃ፡-
https://linktr.ee/ethiopianenterprisedevelopment