
የፋሲካ ባልትናና ቅመማ ቅመም የጥራትና የስኬት ጉዞ ፦ ከባልትና ምርት ወደ ምርምር ማዕከል የግንባታ ራዕይ ጉዞ
EED ግንቦት 20/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የምግብ ባህል በደመቁና ልዩ ጣዕም ባላቸው ቅመማ ቅመሞች የታወቀ ነው። ይህንን ባህላዊ ጣዕም ጠብቆ፣ በጥራትና በከፍተኛ ደረጃ አዘጋጅቶ ለገበያ ማቅረብ ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄና ዘመናዊ አሰራርን ይጠይቃል። በተለይም በሀገራችን የሆቴልና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እያደገ በመጣበት በአሁኑ ወቅት፣ ለትልልቅ ሆቴሎችና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ለጠበቁ መስተንግዶዎች አስተማማኝና ጥራት ያለው የባልትና ምርት ማቅረብ የገበያው ወሳኝ ፍላጎት ሆኗል። ይህንን ክፍተት በከፍተኛ ብቃት በመሙላት በዘርፉ ግንባር ቀደም ስም መሆን የቻለው ፋሲካ ባልትናና ቅመማ ቅመም ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ማዕከል በሆነው ሳሪስ አካባቢ ዋና የምርት ማዕከሉን አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ፋሲካ ባልትና በ5 ወንድምና እህቶች እና በ50 ሺህ ብር ካፒታል በ2006 ዓ.ም ስራ የጀመረው ስራ ዛሬ ላይ 90 ሚልየን ብር በማንቀሳቀስ ለ108 ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር ችሏል።
ፋሲካ ባልትናና ቅመማቅመም ጠንካራ መሠረት ያለው የቤተሰብ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዝ ነው። ኢንተርፕራይዙ እንደ አንድ የቤተሰብ ስራ ከመጀመሩ ባሻገር የቤተሰብ አባላት ለስራው ያላቸው ትጋት፣ ሙያዊ ክህሎትና ትውፊታዊ እውቀት ዛሬ ለደረሰበት ከፍተኛ ደረጃና አስተማማኝነት ዋነኛ ምሰሶ ሆኗል።

የፋሲካ ባልትና ልዩ መለያው የወቅታዊ በዓላት ገበያን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን፣ ዓመቱን ሙሉ ከፍተኛ ጥራትና ቀጣይነት ያለው አቅርቦት ለሚፈልጉ ከትልልቅ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችጋር በቋሚነት መስራቱ ነው። ትልልቅ ሆቴሎች በምግብ ጥራትና በንፅህና አጠባበቅ ላይ ያላቸው መመዘኛ በጣም ጥብቅ በመሆኑ፣ ፋሲካ ባልትና ይህንን መስፈርት አሟልቶ የብዙዎቹ ቀዳሚ ምርጫ መሆን ችሏል።
ፋሲካ ባልትና እና ቅመማ ቅመም ዛሬ ላይ ካለው የአቅርቦትና የገበያ መሪነት ባሻገር ወደፊት የዘርፉን ዕድገት ወደ ላቀ ሳይንሳዊ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅና አርቆ አሳቢ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ኢንተርፕራይዙ በምርት ጥራት፣ ደህንነትና አዳዲስ ምርቶች ልማት ላይ በስፋት ለመስራት ትልቅ የቅመማቅመም ምርምርና ስርፀት (R&D) ማዕከል የማቋቋም ራዕይ ሰንቆ እየሠራ ይገኛል።

ይህ ማዕከል ሲቋቋም የኢትዮጵያን ባህላዊ ቅመማቅመሞች ሳይንሳዊ ይዘትና የጤና ጥቅሞች በጥናት በመደገፍ፣ ለሆቴል ኢንዱስትሪው የሚቀርቡ ምርቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ሰፊ ፋይዳ ይኖረዋል።
ባልትናን በሻማ አሽጎ ከመሸጥ የተነሳው ይህ የባልትናና ቅመማቅመም ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዝ፣ የረጅም ጊዜ ልምዱንና ዘመናዊ አሰራርን በማጣመር በኢትዮጵያ የሆቴል አቅርቦት ዘርፍ ላይ ትልቅ አሻራ ማሳረፍ ችሏል። ምርትን ወቅታዊ በዓላት ላይ ብቻ ሳይገድብ፣ የትልልቅ ሆቴሎችን ከፍተኛ መመዘኛ አሟልቶ በቋሚነት ማቅረቡ ለሌሎች ኢንተርፕራይዞችም ትልቅ ምሳሌ ነው። ወደፊት የሚገነባው የምርምር ማዕከልም ለሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትልቅ ኩራትና ተስፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት
#ለተጨማሪ_መረጃ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻችንን ይጎብኙ!
https://linktr.ee/ethiopianenterprisedevelopment