ETHIOPIAN ENTERPRISES DEVELOPMENT

Empowering Manufacturing SMEs for National Economic Transformation and Societal Prosperity !

“በግብርና ምርቶች ላይ ዕሴት መጨመር ካልቻልን ለትውልድ ተሻጋሪ ሀብት ማፍራት አንችልም!”

ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር

EED የካቲት 10/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት አመራርና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ባለሀብቶች በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ በአርባ ምንጭ ከተማ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ተጠናቀቀ።

በመድረኩ የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ  እንደገለፁት በግብርና ምርቶች ላይ ዕሴት በመጨመር ለትውልድ ተሻጋሪ ሀብት ማፍራት እንዲቻል የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽ ኢኒሽየቲቭ በማዘጋጀት ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለው የአምራች ኢንተርፕራይዞች እንቅስቃሴ የሚበረታታ ቢሆንም ክልሉ ካለው የግብርና ፀጋ አንፃር ሲታይ ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል ያሉት ዶ/ር አለባቸው አምራች ኢንተርፕራይዞች በስራ ሂደት ለሚገጥማቸው ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ከመንግስት እንዲሠጣቸው መጠበቅ እንደሌለባቸው አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ ወደ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ አዲስ ለሚገቡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ያሉ ሀገራዊና ክልላዊ ምቹ ሁኔታዎች፤ የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ኢኒሺየቲቭ፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት አፈጻጸም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አምራች ኢንተርፕራይዝ ሆኖ ለመውጣት  የማምረቻ ቦታና የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ከተሳታፊዎች አስተያየት ቀርቦ ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በመድረኩ ከ91 በላይ ባለሀብቶች በአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ለመሠማራት ለክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የንግድ እቅድ አቅርበው ርክክብ ተካሂዷል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

News