ETHIOPIAN ENTERPRISES DEVELOPMENT

Empowering Manufacturing SMEs for National Economic Transformation and Societal Prosperity !

በዓለም አቀፍ ገበያ (ኤክስፖርት) አሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ የምክክር መድረክ ተካሄደ

EED ሐምሌ 29/ 2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ያዘጋጀውና አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በዓለም አቀፍ ገበያ (ኤክስፖርት) ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር በአሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሄደ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ በመድረኩ እንደተናገሩት  መንግስት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ  ልዩ ትኩረት መሰጠቱና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የማኑፋክቸሪንግ ካውንስል አቋቁሙ በልዩ ሁኔታ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ምርቶቻቸውን ወደውጭ ሀገራት የሚልኩ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱና በልዩ ሁኔታ እንዲደገፉ ልማት መ/ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል

ይህ መድረክ የተዘጋጀውም በኤክስፖርት አሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመለየትና ለመቅረፍ እንዲሁም ተቀራርቦ በመስራት ውጤት ለማምጣት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ሀሳባቸውንና ጥያቄዎቻቸውን በተደራጀ አግባብ ማቅረብ እንዲችሉ፣ ይበልጥ ተሰሚነት እንዲኖራቸውና የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንዲቀረፉ በዘርፍ ማህበራት እንዲደራጁም ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች በበኩላቸው ከማምረቻ ቦታ፣ ከፋይናንስ፣ ከምርት ደረጃና ምስክር ወረቀት፣ ከካርጎ አገልግሎትና ጉምሩክ አሰራር ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እንዲቀረፉላቸው ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ከማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችና ከተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመስራት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ኢንተርፕራይዞች በዓለም አቀፍ ገበያ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

በመድረኩ የዓለም አቀፍ ገበያ ያለፉት ዓመታት አፈጻጸምና የቀጣይ እቅድ፣ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች በተመለከተ የመወያያ ሰነዶች ቀርቦ ውይይት ተካሂዷባቸዋል::

በመድረኩ ምርቶቻቸውን ወደውጭ ሀገራት የሚልኩ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች፣ ከዘርፍ ማህበራት ም/ቤት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩትና ሌሎች አስፈጻሚና ባለድርሻ አካላት የመጡ የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

ተጨማሪ መረጃ፡-

#ድረ_ገጽ: https://www.manuf-sme.gov.et

#ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/Ethiopianenterprisedevelopment

#ቴሌግራም፡ https://t.me/ethiopianenterprisedevelopment

#ዩትዩብ፡ https://youtube.com/@ethiopiaenterprise

#ኢሜል: ethiopianenterprise@gmail.com

News