አቶ ጳውሎስ በርጋ፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር

“አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው!”
አቶ ጳውሎስ በርጋ፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር
EED ሐምሌ 29/ 2017 ዓ.ም
አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግና በአሰራርና በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ያለመ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ በ2022 ዓ.ም ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ለማሳካት አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።
ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የገቢ ምርቶችን በመተካት፣ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጪ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን መሠረት ለማስፋትና ለማዘመን የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣት የላቀ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው ለማስቻል በፌደራልና በክልሎች ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ም/ዋና ዳይሬክተሩ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ በአሰራርና በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመለየትና በመፍታት ረገድ የተቀናጀና ዘላቂ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በዚህም መሰረት ባለድርሻ አካላት በጋራ በመስራት ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አቶ ጳውሎስ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከር፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግና በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ጳውሎስ ይህም ውጤት እንዲያመጣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ፣ ሁሉም አካላት በጋራ በመስራት ፤ የተግዳሮቶችን መፍትሄ በመፈለግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በመድረኩ የዘርፉ አስፈጻሚና ባለድርሻ ተቋማት እንዲሁም ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉ ሲሆን በዓለም አቀፍ ገበያ ያለፉት ዓመታት አፈጻጸምና የቀጣይ እቅድ፣ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች ተግዳሮቶች በተመለከተ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ነው::
#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት
ተጨማሪ መረጃ፡-
#ድረ_ገጽ: https://www.manuf-sme.gov.et
#ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/Ethiopianenterprisedevelopment
#ቴሌግራም፡ https://t.me/ethiopianenterprisedevelopment