
“ከዕድል ይልቅ በምርት ጥራት ላይ የተመሠረተ ተወዳዳሪነትን በማፅናት ዘላቂ ገበያ መፍጠር ይገባል!”
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ
EED ጥር 6/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በምርት ጥራት ሰርተፊኬሽን የሚያበቃ ጥራቱን የጠበቀ የአመራረት ስርዓት ላይ ስልጠና እየሰጠ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ የስልጠናውን ሂደት በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት የልማት መስሪያ ቤቱ ከቢዝነስ ፕላን ዝግጅት አንስቶ በምርት ሂደትና ከምርት በኋላም በገበያ ልማት አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ሁሉ በመስጠት በሃገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማስቻል እንደተቋቋመ ገልፀዋል።
በዚህ ሂደትም ጥራት ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ አንፃር መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ አምራች ኢንተርፕራይዞች የምርት ጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬሽን መያዝ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ዶ/ር አለባቸው አያይዘው አሳስበዋል።

አምራች ኢንተርፕራይዞች በዚህ ስልጠና ያገኙትን ክህሎት እንደ ዓይን መግለጫ በመጠቀምና ለሌሎችም በማካፈል ከዕድል ይልቅ በምርት ጥራት ላይ የተመሠረተ ተወዳዳሪነትን በማፅናት ዘላቂ ገበያ መፍጠር እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተር አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በበኩላቸው ስልጠናው አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በስታንዳርዱ መሰረት ደረጃውን የጠበቀ ምርት ማምረት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ያለመ በመሆኑ አምራች ኢንተርፕራይዞች ወደዚህ አሰራር እንዲገቡ እንደሆነ የልማት መስሪያ ቤቱ እንደ አስፈላጊነቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች ያገኙት ስልጠና በሀገር ውስጥና በውጪ ገበያ በሚያመርቷቸው ምርቶች ተወዳዳሪ ሆነው መቀጠል እንዲችሉ እንደሚያስችላቸውና ሙሉ ለሙሉ እንደሚተገብሩት ገልፀው፤ ለስልጠናው ምስጋናቸውን አቅርበዋል:: ተቋሙ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት