
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በመልሶ መጠቀም (Recycling) ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ
EED መጋቢት 8/2018 ዓ.ም (አዲስ አበባ)
ፔትኮ ኢትዮጵያ ‹‹ዓለም አቀፍ የመልሶ መጠቀም ቀንን›› ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀውና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በመልሶ መጠቀም ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማነሳሳት የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ የመልሶ መጠቀም ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥርና ከውጭ የሚገቡ ጥሬ እቃዎችን መተካት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቆሻሻ በአግባቡ ከተያዘና ጥቅም ላይ ከዋለ እድልና ሀብት መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በመልሶ መጠቀም ዘርፍ እንዲሰማሩና ውጤታማ እንዲሆኑ ጥናትን መሰረት ያደረገ ድጋፍ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
ቆሻሻን ወደሀብት የመለወጥ አስተሳሰብን መገንባት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ አብዱልፈታ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዘርፉ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፔትኮ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ምህረት ተክለማርያም በበኩላቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የመልሶ መጠቀም ቀጣይነት ያለው የስራ እድል መፍጠሪያ ዘርፉ መሆኑን በመረዳት በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማስቻል ግንዛቤና መነሳሳት ለመፍጠር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች በመልሶ መጠቀም ዘርፍ እንዲሰማሩና በተለይም ለወጣቶችና ሴቶች ዘላቂ የስራ እድል እንዲፈጥሩ ለማስቻል በማብቃት ፕሮግራም አማካኝነት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ በመልሶ መጠቀም ዘርፍ ያሉ እድሎች፣ ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ በፔትኮ ኢትዮጵያ ማብቃት ፕሮግራም ሲኒየር ዳይሬክተር በሆኑት በዶ/ር አየለ ሄጌኖ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷበታል፡፡
#PETCO_Ethiopia #EED #Global_Recycling_Day
#ኢትዮጵያ_ታምርት_እኛም_እንሸምት https://linktr.ee/ethiopianenterprisedevelopment