ETHIOPIAN ENTERPRISES DEVELOPMENT

Empowering Manufacturing SMEs for National Economic Transformation and Societal Prosperity !

‹‹የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽንን ተግባራዊ ለማድረግና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  የአመራሩ ሚና የጎላ ነው››

አቶ ጳውሎስ በርጋ፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና/ ዳይሬክተር

(ታህሳስ 02/2017 .ም፣ ወራቤ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የአምራች ዘርፍ ንቅናቄ ስራዎችን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በወራቤ ከተማ ውይይት እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና/ ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ ያለ አምራች ኢንዱስትሪ በሀገር ደረጃ ዘላቂ ልማት ማምጣት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ሀገራችንን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተምሳሌት ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የክልሎች ሚናም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ም/ዋና ዳሬክተሩ አክለውም የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽንን ተግባራዊ ለማድረግና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአመራሩ ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸው እንደ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ ወደ መሬት ለማውረድና በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ተግባራዊ በማድረግ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ በዘርፉ ያላቸውን አቅም እንዲለዩና አሟጠው እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ጳውሎስ አመራሩ ቁርጠኛ በመሆን እንዲሰራም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው አምራች ዘርፍ በምርትና ምርታማነት የሚጫወተው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳደግ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ላይ እሴት በመጨመር ጥራት ያለውን ምርት በአካባቢ ለማምረት ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።

በመድረኩ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሰነዶች በዘርፉ ባለሙያዎች የቀረበ ሲሆን የአምራች ዘርፉ የስራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሆሳዕና ዲስትሪክት፣ የደቡብ ካፒታል ን/ስ/አ/ማ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ወልቂጤ ቅርጫፍ የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

News