ETHIOPIAN ENTERPRISES DEVELOPMENT

Empowering Manufacturing SMEs for National Economic Transformation and Societal Prosperity !

የልማት መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞች 129ኛውን የአድዋ ድል በዓልን አከበሩ

EED የካቲት 24/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አመራርና ሰራተኞች “አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል!” በሚል መሪ ቃል 129ኛውን የአድዋ ድል በዓልን በፓናል ውይይትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብረዋል፡፡

የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት ጀግኖች አያቶቻችን ዘመናዊ ትጥቅ ሳይኖራቸው ባላቸው ሃገራዊ ፍቅርና ወኔ በመነሳሳት ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል በማድረግ በፈፀሙት ታላቅ ጀግንነትና በከፈሉት መስዕዋትነት አኩሪ ድል በማስመዝገብ ነፃ ሀገር አስረክበውናል ብለዋል፡፡

እኛም የድል በዓሉን ስናከብር የሀገርን ሰላም በማስጠበቅ በተሰማራንበት የስራ መስክ ሁሉ ድል በማስመዝገብ ታላቅ ሀገር የመገንባት ተልዕኳችንን መወጣትና የተከበረች ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዕለቱ በዓሉን የሚዘክር የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የተቋሙ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ተ/ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮቤል አህመድ የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካውያን ጥቁር ህዝቦች አኩሪ ድል በመሆን ጀግኖች አባቶቻችን የውጭ ወራሪዎችንና የሀገር ውሰጥ ባንዳዎችን ከንቱ ምኞት ያመከኑበት፣ ደምና አጥንታቸውን ከስክሰውና የህይወት መሰዋዕትነት ከፍለው ታሪካዊ ገድል የፈፀሙበት በመሆኑ ታሪክ ሁሌም ሲዘክራቸው ከመኖሩም ባሻገር ትውልዱም በሚገባ ሊረዳው እንደሚገባ አብራርተዋል።

የአሁኑ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩአትን ሀገር ከነ ሙሉ ክብሯ ጠብቆ በማቆየት ለቀጣይ ትውልድ ማሰተላለፍ ከሁላችንም የሚጠበቅ የትውልድ አደራ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን የአድዋ በዓል ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተጠራርተው ባርነትን አንቀበልም፤ ቅኝ መገዛትን አንሻም፤ ብለው በአንድነት እንደተመሙበት ሁሉ የዛሬው ትውልድ የኢኮኖሚ ጥገኛ ሆኖ በእጅ አዙር ቅኝ ላለመገዛት የኢንዱስትሪ አርበኛ በመሆን የኢኮኖሚ ነፃነታችንን ለማወጅ በመተባበርና በአንድነት መስራት እንደሚገባው ተጠቅሷል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት!

News