
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት ድጋፍ ለሚደረግላቸው ወላጆች የልብስ ስፌት ስልጠና በመስጠት አስመርቋል
EED መጋቢት 05/ 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በተቀሙ ወርክሾፕና ባሉት ባለሙያዎች ከተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት ለመጡና የልጆቻቸውን የህክምና ሂደት በመከታተል ላይ ለሚገኙ ወላጆች ለ20 ቀናት መሰረታዊ የልብስ ስፌት ስልጠና በመስጠት አስመርቋል።
የስልጠናው ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ እንደገለፁት ተቋሙ የልማት መ/ቤቱ በተለያዩ ጊዚያት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከድርጅቱ ለመጡና በችግር ላይ ላሉ ወላጆች የሙያ ስልጠና እንዲወስዱ ማመቻቸቱን ተናግረዋል።
ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን ክህሎት ወደ ቋሚ ስራ በመቀየር በሚያገኙት ገቢ እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማገዝ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም ለድርጅቱ 2 የልብስ ስፌት ማሽን፣ የጣቃ ጨርቅና የተለያዩ የስፌት ክሮችን ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሳራ ኢብራሂም በበኩላቸው እንደገለፁት ስልጠናው ልጆቻቸውን በማስታመም የተጠመዱ ወላጆች ከጭንቀታቸው እንዲወጡና ቋሚ ገቢ በሚያስገኝ ስራ እንዲሰማሩ በማሰብ የተመቻቸ መሆኑን ጠቁመው ስልጠናውን ለሰጠው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ስልጣኞች በሰጡት አስተያየት የልብስ ስፌት መሠረታዊ ክህሎት ማግኘታቸውንና ያገኙትን እውቀት ወደ ስራ እንደሚቀይሩት በመግለፅ ዕድሉን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።
በስልጠናው 10 ወንድና 5 ሴቶች በድምሩ ለ15 ወላጆች ለ20 ቀናት በንድፈ-ሀሳብና ተግባር የተደገፈ መሠረታዊ የልብስ ስፌት ስልጠና የወሰዱ ሲሆን ሰልጣኞች የስልጠና ሰርተፍኬት አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከዚህ ቀደም የአረጋዊያንን ቤት በመገንባት፤ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ማዕድ በማጋራት፤ ተማሪዎችን በማስተማር እንዲሁም ችግኝ በመትከልና ደም በመለገስ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።