
“ዘርፉን ለመደገፍ የተዘጋጁ ሰነዶች ተግባራዊ ሆነው ውጤት እንዲያመጡ ተገቢውን ግንዛቤ በመያዝና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር መፈፀም ይገባል!”
ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ፣ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር
EED የካቲት 29/2017ዓ.ም (አዳማ)
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አምራች ዘርፉን ለመደገፍ በተዘጋጅ ስትራቴጂዎች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ስርዓቶች ላይ ለዘርፉ መካከለኛ አመራሮች “የላቀ አቅም የላቀ ፈጠራ፣ ፍጥነትና ተነሳሽነት ለኢንተርፕራይዝ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ በስልጠናው ማጠቃለያ እንደተናገሩት የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፉን መሰረት ማስፋት እንዲቻል እስከ ገጠር ድረስ ወርዶ መስራት ያስፈልጋል ለዚህም የገጠር ኢንደስትሪያላይዜሽን ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል።
ይህም የአካባቢን ፀጋ ለግብዓትነት መጠቀም እንዲቻል፣ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ማምረትና በየአካባቢው የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት ውጤታማ እንዲሆኑ ችግሮቻቸውን በተገቢው ሁኔታ መፍታትና አቅም አጠቃቀማቸውን የሚያጎለብቱ ድጋፎችን ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል::

ዘርፉን ለመደገፍ የተዘጋጁ ሰነዶች ተግባራዊ ሆነው ውጤት እንዲያመጡ ተገቢውን ግንዛቤ በመያዝና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር መፈፀም ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ በበኩላቸው እንደገለፁት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በአደጉ እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ለውጥ እያመጣ ያለ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፉን ለመደገፍ የተዘጋጁ ስትራቴጅዎች፣ መመሪያዎችና የአሰራር ስርዓቶችን በሚገባ በመረዳት ወደውጤት ለመቀየር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተቋሙን ዌብ ፖርታል (www.manuf-sme.gov.et) ማስተዋወቅ የተቻለ ሲሆን ዌብ ፖርታሉን አስፈላጊ የዘርፉን መረጃዎች በመጫን ጥቅም ማዋል እንደሚገባ በመግለፅ የአሰራር ሂደቱ ላይ ለሰልጣኞች ገለፃ ተደርጓል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት