ETHIOPIAN ENTERPRISES DEVELOPMENT

Empowering Manufacturing SMEs for National Economic Transformation and Societal Prosperity !

“የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ያልተስፋፋበት ሀገር የማደግ ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው!”

አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ዋና ተጠሪ

EED የካቲት 10/2017 ዓ.ም  (አርባ ምንጭ)

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአምራች ዘርፉ አመራርና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ባለሀብቶች ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ኢትዮጵያ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እያደረገች ባለው የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች፤ በተለይ ብዙሀኑን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ባለው ስራ በቀላሉ ዕሴት በመጨመር፣ ለዜጎች የስራ ዕድል ለሀገር ደግሞ ሀብት መፍጠር ከሚችሉ ዘርፎች አንዱ አምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ በመሆኑ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አምራች ዘርፉ ከግብርና እና ማዕድን ዘርፍ ጋር በቀጥታ በግብዓት ዓቅርቦት በመመጋገብና አምራችነትን ተከትሎ በሚመጣ ተዛማጅ የመሰረተ ልማት ስራዎች የህዝባችንን የመልማት ጥያቄ በአጭር ግዜ መመለስ የሚችል ዘርፍ ነው ያሉት አቶ ገ/መስቀል፣ እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አብዛኛው ኢኮኖሚያቸው በግብርና ምርት በሆኑት በፍራ ፍሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራ ጥሬዎች፣ እንስሳት እርባታ እንዲሁም ማዕድን ላይ መሰረት ላደረጉ ክልሎች ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

አቶ ገብረመስቀል አክለውም ክልሉ በስራ ወዳድነት ባህሉ የሚታወቅ በከፊል የተማረ የሰው ሀይል፣ በቂ የግብርና እና የማዕድን ምርት መኖሩ፣ ምቹ የፋይናንስ አቅርቦት መኖሩ እንዲሁም ሰላማዊ አካባቢ በመሆኑ ዜጎች ትንሽ አውጥተው ብዙ የሚያተርፉበት አካባቢ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ ያልተስፋፋበት ሀገር የማደግ ዕድሉ በጣም ጠባብ መሆኑን የገለጹት አቶ ገብረመስቀል በክልሉ በአምራች ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ መዋዕለ ነዋያችሁን በማፍሰስ እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁ አምራች ኢንተርፕራይዞች ከራሳችሁ አልፎ ለሀገር ብልፅግና የበኩላችሁን እያዋጣችሁ በመሆኑ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ይህን መድረክ በማዘጋጀቱ አመስግነው ክልሉ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት!

News