የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብር አቶ መላኩ አለበል

“አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ ነው!”
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብር አቶ መላኩ አለበል
EED መጋቢት 18/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት አፈጻጸም ዙሪያ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብር አቶ መላኩ አለበል የሀገራት መነሻና ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች መሆናቸውንና አምራች ኢንተርፕራይዞች ከስራ ዕድል መፍጠሪያነት ባለፈ ሀብት ለመያዝና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
በአደጉት ሀገራት ከ80 በመቶ በላይ የሚፈጠረው የስራ ዕድል በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መሆኑን የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትሩ በሀገራችን ባለፉት 6 አመታት ዘርፉን ለመደገፍ የጠለያዩ ስራዎችን በተለይ የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተፈጠረ ቅንጅት ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሲታሰብ በዋናነት አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዋንኛ መሰረቶች ናቸው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የኢንተርፕራይዞችን ዘላቂነትና ተወዳዳሪነት ከማሳደግ አኳያ የፋይናንስ አቅርቦት ጉዳይ የሚኖረው ድርሻ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡
የአምራች ኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ከአለም ባንክ ጋር በተደረገ ስምምነት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት በኩል ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናስ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግና ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ክቡር አቶ መላኩ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋታል፣ ዕድገት ያስፈልጋታል፤ ተወዳዳሪና ዘላቂ ልማት ያስፈልጋታል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ይህንን ማሳካት የሚቻለው ለዜጎች ዘላቂ የሆነ ሰላም ማምጣት የሚችል የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለዜጎች የመለወጥ ተስፋ በመስጠት መሆኑንና ለዚህም አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በአግባቡ መደገፍና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ ኢትዮጵያን የመደገፍ ስራ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጡ ክቡር ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ የአነስተኛና መካከለኛ ፋይናንስ ፕሮጀክት አፈፃፀምና በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ ፕሮጀክት ያመጣው ለውጥ ጥናት (impact assessment) ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት!