ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ ፤ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር

“የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ መሆን የሚችል የላቀ አፈፃፀም ያለው ፕሮጀክት ነው!”
ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ ፤ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር
EED መጋቢት 19/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት ከሚያበረክተው የላቀ አስተዋፅኦ አንፃር፤ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ በመድረኩ እንደገለፁት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ መሆን የሚችል የላቀ አፈፃፀም ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
በተለይም ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ፕሮጀክቱ ውጤታማ መሆኑን የገለልተኛ ወገን በሆነው በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተደረገው ጥናት ማሳየቱንና ይህም የበርካታ ተቋማት ቅንጅት ውጤት መሆኑን ገልፀዋል::

ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ባለፉት ዓመታት በተለይም በሊዝ ፍይናንስ በርካታ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚና ተወዳዳሪ መሆናቸውንም ገልፀዋል::
በቅርቡ የተጀመረው የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽንና ትራንስፎርሜሽን ኢኒሽየቲቭ የአምራች ዘርፉን መሰረት ሰፊ ለማድረግና የኢንዱስትሪ ጥሬ ግብአትና የሰው ሃይል ወደ አለበት የገጠሩ የሀገራችን ክፍል ለማስፋት እንደሚጠቅም የገለፁት ዶ/ር አለባቸው በጥናት የተረጋገጠው እና ከፋይናንስ ፕሮጀክቱ ያገኘነውን ልምድ የሚያሳየው፤ ኢኒሺየቲቩን ስኬታማ ማድረግ የሚቻለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ከስልጠና ጋር በማቀናጀት መስጠት ሲቻል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ የኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚንስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንዲሁም የሊዝ ፋይናንስ ማህበር አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ተሳትፈውበታል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት